፭
፩ ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ፪ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። ፫ በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። ፬ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። ፭ በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ፮ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው። ፯ ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ፰ ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ፱ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ፲ ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት። ፲፩ እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። ፲፪ እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ፲፫ ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ፲፬ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ፲፭ ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ፲፮ ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ፲፯ ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ፲፰ እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ፲፱ ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። ፳ አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። ፳፩ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ፳፪-፳፬ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። ፳፭ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። ፳፮ አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። ፳፯ የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። ፳፰-፴ እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። ፴፩ እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ ፴፪ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ። ፴፫ እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል። ፴፬ እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። ፴፭ እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። ፴፮ እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። ፴፯ የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤ ፴፰ እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። ፴፱ እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ፵ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ፵፩-፵፫ እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። ፵፬ እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? ፵፭ እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ፵፮ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። ፵፯ መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?
<- የዮሐንስ ወንጌል 4የዮሐንስ ወንጌል 6 ->