፲
፩ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። ፪ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ፫ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። ፬ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ። ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው። ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። ፭ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። ፮ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል። ፯ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ፰ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው። ፱ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። ፲ ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ፲፩ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ ፲፪ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ፲፫ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ፲፬ ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ። ፲፭ ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ፲፮ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ፲፯ ጴጥሮስም ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ፲፰ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን? ብለው ይጠይቁ ነበር። ፲፱ ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ፳ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው። ፳፩ ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው? አላቸው። ፳፪ እነርሱም። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት። ፳፫ እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። ፳፬ በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ፳፭ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ፳፮ ጴጥሮስ ግን። ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው። ፳፯ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ። ፳፰ አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ፳፱ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ አላቸው። ፴ ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። ፴፩ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። ፴፪ እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል አለኝ። ፴፫ ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን። ፴፬-፴፮ የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ፴፯ ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። ፴፰ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ ፴፱ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። ፵ እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ፵፩ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። ፵፪ ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። ፵፫ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ፵፬ ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ፵፭ ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ ፵፮ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። ፵፯ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። ፵፰ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
<- የሐዋርያት ሥራ 9የሐዋርያት ሥራ 11 ->